Numbers 8

የመብራቶቹ አቀማመጥ

1 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2“አሮንን ተናገረው፤ እንዲህም በለው፤ ‘ሰባቱን መብራቶች በየቦታቸው በምታስቀምጥበት ጊዜ በመቅረዙ ፊት ለፊት ላለው አካባቢ ብርሃን ይሰጣሉ።’ ”

3አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት መብራቶቹ በመቅረዙ ላይ ሆነው ፊት ለፊት እንዲያበሩ አስቀመጣቸው። 4የመቅረዙ አሠራር እንዲህ ነበር፤ ከመቆሚያው እስከ አበቦቹ ያለው ከተቀጠቀጠ ወርቅ የተሠራ ሲሆን፣ የመቅረዙም አሠራር እግዚአብሔር (ያህዌ) ለሙሴ ባሳየው መሠረት ነበር።

የሌዋውያን ለአገልግሎት መለየት

5 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6“ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን መካከል ለይተህ በሥርዐቱ መሠረት አንጻቸው። 7ስታነጻቸውም እንዲህ አድርግ፤ በሚያነጻ ውሃ እርጫቸው፤ ገላቸውን በሙሉ ተላጭተው ልብሳቸውን ይጠቡ፤ በዚህም ይንጹ። 8በዘይት ከተለወሰ ልም ዱቄት የእህል ቍርባን ጋር አንድ ወይፈን ይውሰዱ፤ ከዚያም ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን ሌላ ወይፈን አንተ ትወስዳለህ። 9ሌዋውያኑን ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት አምጣ፤ መላውንም የእስራኤል ማኅብረ ሰብ ሰብስብ፤ 10ሌዋውያኑን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቅርብ፤ ከዚያም እስራኤላውያን እጃቸውን ይጫኑባቸው። 11ከዚያም አሮን ሌዋውያኑን የእግዚአብሔርን (ያህዌ) አገልግሎት ለማከናወን ዝግጁ እንዲሆኑ ከእስራኤላውያን መካከል እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ያቅርባቸው።

12“ሌዋውያኑ እጃቸውን በወይፈኖቹ ራስ ላይ ከጫኑ በኋላ ለሌዋውያኑ ማስተስረያ ይሆኑ ዘንድ የኀጢአት መሥዋዕት፣ ሌላውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው። 13ከዚያም ሌዋውያኑን በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህም ለእግዚአብሔር (ያህዌ) አቅርባቸው። 14በዚህ መሠረት ሌዋውያኑን ከእስራኤላውያን ትለያቸዋለህ፤ እነርሱም የእኔ ይሆናሉ።

15“ሌዋውያኑን ካነጻሓቸውና እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት አድርገህ ካቀረብሃቸው በኋላ አገልግሎታቸውን ለመፈጸም ወደ መገናኛው ድንኳን ይመጣሉ፤ 16እነርሱም ሙሉ በሙሉ የእኔ እንዲሆኑ የተሰጡኝ እስራኤላውያን ናቸው፤ ከማንኛዪቱም እስራኤላዊት በተወለደ በኵር ወንድ ልጅ ምትክ የራሴ እንዲሆኑ ወስጃቸዋለሁ። 17ከሰውም ሆነ ከእንስሳ በእስራኤል የተወለደ ማንኛውም በኵር ተባዕት የእኔ ነው፤ በግብፅ የነበረውን በኵር ሁሉ በመታሁ ጊዜ የእኔ እንዲሆኑ ለይቻቸዋለሁ። 18በእስራኤል በተወለዱት ተባዕት በኵሮች ሁሉ ምትክም ሌዋውያኑን ወስጃለሁ። 19እስራኤላውያንን ወክለው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት እንዲያከናውኑና እስራኤላውያን ወደ ተቀደሰው ስፍራ ቢቀርቡ እንዳይቀሠፉ ያስተሰርዩላቸው ዘንድ፣ ከእስራኤላውያን ሁሉ መካከል ሌዋውያኑን ስጦታ አድርጌ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻቸዋለሁ።” 20ሙሴና አሮን እንዲሁም የእስራኤል ማኅበረ ሰብ ሁሉ እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት በሌዋውያኑ አደረጉ። 21ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሶቻቸውንም ዐጠቡ፤ ከዚያም አሮን እንደሚወዘወዝ መሥዋዕት በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አቀረባቸው፤ እንዲነጹም ማስተስረያ አደረገላቸው። 22ከዚህ በኋላ ሌዋውያኑ በአሮንና በልጆቹ ኀላፊነት ሥር ሆነው ድንኳን ውስጥ የሚፈጸመውን አገልግሎት ለማከናወን ገቡ። እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን ባዘዘው መሠረት አስፈላጊውን በሌዋውያኑ አደረጉ።

23 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ 24“ሌዋውያንን የሚመለከተው ደንብ ይህ ነው፤ በመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ለመሳተፍ ሃያ አምስት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንዶች ይመጣሉ፤ 25ዕድሜያቸው አምሳ ዓመት ሲሞላ ግን መደበኛ አገልግሎታቸውን ይተዉ፤ ዳግም ሥራ አይሥሩ። 26ከዚያ በኋላ ወንድሞቻቸው በመገናኛው ድንኳን ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ ያግዟቸዋል እንጂ ራሳቸው መሥራት የለባቸውም። ኀላፊነታቸውን እንዲወጡ የምታሰማራቸው በዚህ መልኩ ነው።”

Copyright information for AmhNASV